ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ኮሮናን በመከላከል በጥንቃቄ ማክበር አለበት ….. የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር

ሀዋሳ፣ ግንቦት 14/2012 (ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል መንግስት ያወጣውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ በጾም ወቅት በቤቱ ጸሎት ሲያደርግ እንደቆየው ሁሉ በዓሉንም በጥንቃቄ ማክበር እንደሚገባ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

የከተማዋ አስተዳደር ከሲዳማ ዞን እስልምና ምክር ቤት ጋር በመተባበር 250 ደጋፊ የሌላቸው የእስልምና ተከታዮች ለበዓሉና ለአንድ ወር ምግብ የሚሆን የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ አድርጓል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳድር ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ድጋፉን በሰጡበት ወቅት እንዳሉት ህዝበ ሙስሊሙ መንግስት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማክበር በጾም ወቅት በቤቱ ጸሎት በማድረስና ራሱን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ያደረገው አስተዋጽኦ የሚያስመሰግን ነው።

የኮሮና ቫይረስ በሀገራችን ላይ የደቀነው ስጋት ለመከላከል ህዝበ ሙስሊሙ ካደረገው ጥንቃቄ ባሻገር ለዘመናት አብሮነት በቆየው የመተጋገዝና የመረዳዳት ልምዱ መሰረት ደጋፊ የሌላቸው ወገኖቹን በመርዳት ያደረገውም እገዛ ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በጾም ወቅት ከቤት ባለመውጣት በጸሎት ተግታችሁ የበሽታውን ስርጭት ፈጣሪ የተለማመናችሁበትን እገዛ ወደፊትም መቀጠል አለባችሁ ብለዋል።

በዓሉም ረዳት የሌላቸውን ወገኖቻችሁን በማገዝና በማሰብ የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭት እንዳይስፋፋ በጥንቃቄ ማክበር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሲዳማ ዞን ሸሪዓ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሀጂ ቃሲም አደም በበኩላቸው የእስልምና ህግ በሚፈቅደው መሰረት በዓሉን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በማገዝ ማክበር ይገባል።

በአሁኑ ወቅት የአለም ስጋት የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ሁሉም የመጅሊሱን ውሳኔ ተቀብሎ በጾም ወቅት ጸሎቱን በቤቱ ሲያደርግ እንዳሳለፈው ሁሉ በዓሉንም በቤቱ ማሳለፍ እንዳለበት ገልጸዋል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግም የሲዳማ ዞን እስልምና ምክር ቤት ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ከ200 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ ለበዓሉና ለአንድ ወር ቀለብ የሚሆን የእህልና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ለ250 ቤተሰቦች ማበርከቱን ጠቁመዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው ሰዎች ውስጥ አካል ጉዳተኛ የሆኑት አቶ ሀምዛ ጀማል እንደገለጹት የሀዋሳ ከተማ አስተዳደርና የሲዳማ ዞን እስልምና ምክር ቤት ላደረገልን ድጋፍ እናመሰግናለን ብለዋል።

ድጋፉ ከተደረገላቸው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አላነ አበበ በአቅም ማነስ የተነሳ ቀድሞውኑ ሲቸገሩ የነበሩ ቢሆንም በተለይ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ወዲህ የተለያዩ እንቅቃሴዎች በመገደባቸው ተጨማሪ ጫና እንደፈጠረባቸው ገልጸው ለድጋፉ አመስግነዋል።

Related posts

Leave a Comment