ወደ ባህረ ሰላጤው አገራት ለስደት የሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን የጉዳቱን ልክ በደንብ እንደማያውቁ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2012(ኢዜአ) ለሥራ ፍለጋ ወደ ባህረ ሰላጤው አገራት ለስደት የሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን የጉዳቱን ልክ በደንብ እንደማያውቁ አንድ ጥናት አመለከተ።

በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅትና በአውሮፓ ህብረት የሚተገበረው የአፍሪካ ቀንድ የጋራ የስደተኞች ጥበቃ መልሶ ማገናኘት ፕሮግራም ትብብር ‘ዘ ዲዛየር ቱ ትሪቭ ሪጋርድለስ ኦፍ ሪስክ’  በሚል ርዕስ ባካሄደው ጥናት ነው ጉዳዩን ይፋ ያደረገው።

በጥናቱ እንደተገለጸው በምስራቅ የአገሪቱ ክፍል አቋርጠው ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚጓዙ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የጉዞውን አደገኛነት አያውቁም።

ስደተኞቹ በጉዟቸው ለረሃብና የውሃ ጥም ከመጋለጥ ባለፈ የውሃ ወለድ፣ የተላላፊ በሽታ፣ የአንጀት ሕመም እንዲሁም የመብት ረገጣ እንደሚገጥማቸው የማያውቁ ናቸው።

ጥናቱ በጅቡቲ “ኦቦክ” ተቀምጠው ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሻገር የሚጠባበቁ  2 ሺህ ወጣት ኢትዮጵያዊያንን በማነጋገር የተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።

እኤአ ከ2017 አንስቶ 400 ሺህ ኢትዮጵያዊያን የአረብ ባህረ ሰላጤን ማቋረጣቸው በጥናቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት ብቻ 12 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።

በጥናቱ እንደተመለከተው በርካቶቹ ኢኮኖሚያቸውን ለማሻሻል በማለም ስደትን ምርጫቸው ቢያደርጉም  ያሰቡትን አያገኙም።

ከዚህ በተጨማሪ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የሚጠይቋቸው ገንዘብ በርካታ መሆኑ በጥናቱ ተጠቁሟል።

ለስደት የሚነሳሱት በአካባቢያቸው የሚኖሩ ወጣቶች በሚልኩት ገንዘብ የቤተሰቦቻቸው ኑሮ ሲሻሻ በመመልከት መሆኑን ጥያቄ የቀረበለት አንድ ወጣት ተናግሯል።

ከሳዑዲ በሚላክ ገንዘብ ህይወታቸው የተቀየረ ሰዎችን መመልከት ለጉዞ እንደሚያነሳሳቸው የገለጹት ወጣቶቹ በደላሎችና ከስደት ተመላሾች ተረክ በመታለል እንደሚጓዙም ተናግረው ።

በጥናቱ እንደተጠቆመው በስደት ከሚጓዙት መካከል 36 በመቶ የሚሆኑት ወጣት ሴቶች ሲሆኑ 21 በመቶ ወንዶች ናቸው።

በጥናቱ ሁሉም በሚባል ደረጃ ቤተሰቦቻቸው መሰደዳቸውን እንደሚደግፉ የጠቆሙ ሲሆን 64 በመቶ የሚጠጉት ደግሞ ከሁለት ጊዜ በላይ የስደት መንገዱን የተጋፈጡ ናቸው።

ለመጀመሪያ ጊዜ ለስደት ከተዘጋጁት መካከል 59 በመቶ የሚሆኑት ጉዟቸውን በተመለከተ ለቤተሰቦቻቸው መረጃውን እንደማያካፍሉ ተገልጿል።

ከጠቅላላው 83 በመቶ የሚሆኑት ተጓዥች ደግሞ የስደት አማራጭን ተግባራዊ ለማድረግ የሚወስኑት ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ መሆኑን መናገራቸውን ጥናቱ አመላክቷል።

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር መሃመድ አብዲኬር ሪፖርቱን ዋቢ አድርገው እንዳሉት በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን በተሳሳተ መረጃ ላይ በመመስረት አስከፊውን ጉዞ ያደርጋሉ።

” ምንም አይነት ጠንካራ ዝግጅት የላቸውም፤ በቂ መገልገያ ሳይዙ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ይጥላሉ፤ ራሳቸውንም ለብዝበዛና ለከፋ ጉዳት ያጋልጣሉ።” ብለዋል።

ጥናቱ ዕድሜያቸው ከ19 እስከ 29 ዓመት ያሉ ወጣት ኢትዮጵያዊያን በምስራቅ የአገሪቱ ክፍል አድርገው ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚያደርጉት ጉዞ አደገኛ መሆኑን እንዲገነዘቡና የሚያልሙትን ሁሉ ማግኘት እንደማይችሉ ግንዛቤ ለመፍጠር መካሄዱን ተገልጿል።

Related posts

Leave a Comment