በአዳማ ከተማ ከ730 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች የተገኘባቸው አሽከርካሪዎች ተያዙ

አዳማ፣ ግንቦት 14/2012 (ኢዜአ ) በአዳማ ከተማ ከ730 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድና ህገ ወጥ እቃዎች ሲያጓጉዙ የተገኙ ስድስት አሽከርካሪዎች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

የከተማዋ አስተዳደር  ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ረዳት ኢንስፔክተር ወርቅነሸ ገልሜሳ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በግለሰቦቹ ተሽከርካሪዎች ትናንት ሲጓጓዙ ከነበሩት  መካከል  ልባሽ ጨርቆች፣ ሲጋራ፣ ሺሻ እና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ይገኙበታል።

የከተማዋ የፖሊስ አባላት ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን  ለመከላከል ባደረጉት የቁጥጥር ዘመቻ የተገኙት እቃዎቹ በታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3- 28585 ኦሮ በሆነ  የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ተጭነው ወደ አዳማ ከተማ ሲገቡ ነው።

ከዚህም ሌላ 1ሺ 794 ጀሪካን ባለሶስት እና ባለአምስት ሊትር የምግብ ዘይት የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3 -59 7 54 አዲስ አበባ በሆነ አይሱዙ ተሽከርካሪ ላይ በህገ ወጥ መንገድ ተጭኖ  ሲጓጓዝ አዳማ ከተማ ውስጥ  በቁጥጥር ስራ መዋሉን ረዳት ኢንስፔክተሯ ጨምረው ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም  መነሻውን ድሬዳዋ  የሆነ 915 ኩንታል ሲሚንቶ  በአራት  ሲኖ ትራክ ተሳቢ ተሽከርካሪዎች ተጭኖ  አዳማ በማስገባት ሰዎች በየሰፈሩ በማዘዋወር  ሲሸጡ እንደተደረሰባቸው አመልክተዋል።

የኮንትሮባንድና ህገ ወጥ እቃዎችን ሲያጓጉዙ የነበሩ ስድስት አሽከርካሪዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው  መሆኑንም አስታውቀዋል።

Related posts

Leave a Comment