በዓሉ ኮሮናን በመከላከልና የተቸገሩትን በመርዳት ሊከበር ይገባል …. የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳድር

ሰመራ፣ ግንቦት 14/2012 (ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ 1ሺህ 441ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል ሲያከብር እራሱን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የበለጠ ተዘጋጅቶና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ መሆን እንደሚገባው የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ አሳሰቡ ።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ለህዝበ ሙስሊሙ እንኳን ለ1ሺህ  441ኛው ሂጅራ የኢድ አል-ፈጥር በአል አደረሳችሁ የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

ርእሰ-መስተዳድሩ በአሉን አስመልክተው ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አንደተናገሩት የ1ሺህ 441ኛው የኢድ አልፈጥር በአል እራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅና የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመርዳት ልናከብረው ይገባል ብለዋል።

በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመከላከል ስራዎች ላይ ተጠምደን የምናከብረው በመሆኑ አንዱ ለሌላው ጤንነት በማሰብ ጭምር የምናከብረው በአል መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

 ህብረተሰቡ በአሉን ማህበራዊ ርቀቱን ጠብቆ ተገቢውን የደህንነት መጠበቂያ አልባሳት ተጠቅሞ በሀላፊነት መንፈስ እንዲያከብረው መልእክት አስተላልፈዋል።

ረመዳን መረዳዳት፤ አብሮነትና ወንድማማችነት የሚጠናከርበት ወር በመሆኑ ይህንኑ በሚያጠናክር መልኩ በዓሉ ሊከበር እንደሚገባው ርእሰ መስተዳድሩ ምክር ለግሰዋል።

በመሆኑም በበአሉ እለት የእምነቱ ተከታዮች ሁሉም እኩል ተደስተው እንዲያልፉ ያለው  ለሌላው በማካፈልና በመደገፍ መንፈሳዊ አብሮነቱንና ወንድማማችነቱን የሚያጠናክር በጎ ተግባራት በመፈፀም ልናከብረው ይገባል ብለዋል።

በተለይም አቅመ-ደካሞች ፣ አረጋዊያንና ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት እንደማንኛውም ሰው በዓሉን ተደስተው እንዲያሳልፉ ሁሉም የቻለውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በዓሉ ለመላው ሙስሊሙ ህብረተሰብ የደስታ ፣ የሰላምና የአብሮነት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል ።

Related posts

Leave a Comment