ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ለእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14/2012(ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ 1 ሺህ 441ኛውን የኢድ አል ፈጥር በዓል አስመልክተው ለእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የረመዳን ወር ሥጋዊ ፍላጎትን በመንፈሳዊ ጽናት መርታትንና ራስን ማስገዛትን የመማሪያ ወር መሆኑን አስታውሰዋል።

ሰው ከምድራዊ ሕይወቱ ባሻገር ያለውን ሰማያዊ ዓለም በጥቂቱ የሚቀምስበት ወቅት እንደሆነም ነው የገለጹት።

“ብዙዎች ረመዳን ሲገባ በከፍተኛ ደረጃ ደስታ ይሰማቸዋል፤ በአንጻሩ ሲወጣ ደግሞ ያዝናሉ፣ ከአንዳች ከፍታ የወረዱ መስሎ ይሰማቸዋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይም እንደ ዘንድሮ ያለው የረመዳን ጾም በአገሪቱ የተከሰተውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የማሸነፊያ ትልቁ መሳሪያ በመሆኑ ጾሙ ከአዕምሮ እንዳይጠፋ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል። 

“የረመዳን የፆም ወቅትን የተቀበልነውም የምንሸኘውም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከከፈተብን ጦርነት ጋር ፊት ለፊት በተጋጠምንበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ነው “ ሲሉም ገልጸዋል። 

ህዝበ ሙስሊሙ በታላቁ የረመዳን ወር ከመስጊድ ሳይለይ ለማሳለፍ ዓመቱን ሙሉ በጉጉት እንደሚጠብቀው ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዘንድሮ ወረርሽኙ ባስከተለው ተጽዕኖ ምክንያት ይህን ማድረግ አለመቻሉን ተናግረዋል።

ብዙዎች ጾሙን ያሳለፉት እና ስግደቱን የሰገዱት በየቤታቸው በመሆን እንደሆነ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ይሄን ወቅት በትዕግስት፣ በታዛዥነት እና በአርቆ አሳቢነት ላሳለፉ ሙስሊም ወንድም እና እህቶቼ ምስጋና ለማቅብ እወዳለሁ” ብለዋል።

“ህዝባችን ሳይጎዳ ወረርሽኙን እንድናሳልፈው ሲሉ መራር የሆውን ውሳኔ ያሳለፉትን የሃይማኖት አባቶች እና የነርሱን ትእዛዝ ያከበሩትን ሙስሊም ወገኖቻችንን የኢትዮጵያ ታሪክ በኩራትና በአድናቆት ሲያስታውሳቸው ይኖራል” ሲሉም ዶክተር ዐብይ ተናግረዋል።

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና የዜጎችን ህይወት ለመታደግ የረመዳን እሴቶችና ትሩፋቶች የላቀሚና እንዳላቸውም ነው ዶክተር ዐቢይ የገለጹት።

“ጾሙን በሰላም አሳለፎ ለኢድ ያደረሰን ፈጣሪ የወረርሽኙንም ወቅት አሳለፎ ለመልካሙ ጊዜ እንደሚያደርሰን ሙሉ እምነት አለኝ” ብለዋል። 

ቀጣዩን የኢድ አል ፈጥር በዓል ህዝበ ሙስሊሙ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በጸዳ መልኩ እንደሚያከብረው ዶክተር ዐብይ ያላቸውንም ተስፋ ተናግረዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የከፈተውን ጦርነት ከመከላከል ጎን ለጎን የህብረተሰቡን እርስ በርስ የመደጋገፍ ባህል ማጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።

“አቅም በፈቀደ መጠን መአዳችንን እናጋራ፤ ችግረኛ ወገኖቻችንን በእውቀት፣ በገንዘብና በቁስ እንደግፍ፣ አንድነትን የማጠናከር ተግባሮቻችንን ከጾም ወር ውጭ ባሉ አስራ አንድ ወራትም እናዝልቃቸው” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር ዐብይ ገለጻ ኮቪድ-19 በዓለም ላይ ብርቱ ክንዱን በማሳረፍ አደጋ እያደረሰ ያለው ሰዎች ራሳቸውን በመቆጣጠር የመከላከያ መንገዶችን ሳይዘናጉ በአግባቡ መተግበር ባለመቻላቸው ነው።

“ራሳችንን ለሃይማኖት አባቶችና ለጤና ባለሙያዎች ተገዥ ካደረግን፤ ሙስሊሞችም በጾሙ ወቅት ያሳዩትን ብርታትና ቁርጠኝነት ማስቀጠል ከቻሉ ኢትዮጵያ ወረርሽኙን በመቋቋም የምትመሰገን ሀገር ትሆናለች” ሲሉም ገልጸዋል።

ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ከሌሎች እምነቶች ተከታዮች ጋር እያደረጉት ያለው ትብብርና መተሳሰብ ከቀጠለ ወረርሽኙ ለኢትዮጵውያን መማሪያ እንጂ መማረሪያ እንደማይሆንም ዶክተር ዐቢይ በመልዕክታቸው ተናግረዋል።

Related posts

Leave a Comment